የመኖሪያ ፈቃድ እና ዜግነት መቀየር

በስዊዘርላንድ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ለመኖር ወይም እዚህ ለመስራት ፈቃድ ያስፈልጋል። የተለያዩ ዓይነቶች የመቆያ ፈቃዶች እና የመኖሪያ ፈቃዶች መካከል ብዙ ልዩነት አለ።.

የፈቃድ ዓይነቶች

በስዊዘርላንድ በስራ ላይ ያለ ወይም ከ3 ወር በላይ ቆይታ ላደረገ ሰው የመቆያ ፍቃድ ያስፈልገዋል። ይህም ፍቃድ ከካንቶን የስደተኞች አስተዳደር ጽ/ቤት (Migrationsamt) ይሰጣል። በአጭር የመቆያ ፍቃድ (እስከ 1 ዓመት)፣ በመቆያ ፍቃድ (የተገደበ) እና በመኖሪያ ፈቃድ (ያለ ገደብ)፣ እንዲሁም ድንበር የማቋረጥ ፍቃድ መካከል ልዩነት አለ።

  • „ለአጭር ጊዜ የመቆያ ፍቃድ L“ (Kurzaufenthaltsbewilligung L): ይህ ፈቃድ የሚሰጠው ለተገደበ ግዜ (በብዛት ለ1 ዓመት) ለተወሰነ የመቆያ ምክንያት ስዊዘርላንድ ለመኖር ያስችላል። አብዛኛዎቹ ከ EU-/EFTA ሃገር የመጡ ነዋሪዎች ከ 3 ወር እስከ 1 ዓመት ድረስ ስራ (የስራ ውል) ያላቸው መሆኑ ማረጋገጥ ከቻሉ፣ ይህ ፍቃድ እንዲሰጣቸው መብት አላቸው።
  • „የመቆያ ፍቃድ B“ (Aufenthaltsbewilligung B) (እስከ 1 ዓመት): ይህ ፈቃድ የሚሰጠው ለረጅም ጊዜ ስዊዘርላንድ ለሚቆዩ ሰዎች ነው። አብዛኛዎቹ ከ EU-/EFTA ሃገር የመጡ ነዋሪዎች ከ1 ዓመት በላይ ስዊዘርላንድ ውስጥ የሰሩ መሆኑን ማረጋገጥ ከቻሉና (የስራ ውል) ካላቸው፣ ይህንን ፈቃድ የማግኘት መብት አላቸው። ይህ ፈቃድ ከEU/EFTA ለመጡ ነዋሪዎች ለ 5 ዓመት ይሰጣል። ከዚህ ውጪ ከሌላ አገር ለመጡ ሰዎች ግን ለ1 ዓመት የሚቆይ ብቻ ነው የሚሰጣቸው። ከዛ በኋላ ለማራዘም ማመልከት ያስፈልጋል። ይህ ፈቃድ እንዲራዘም ሌሎች መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የጀርመን የቋንቋ ኮርስ ከመማር ጋር ይያያዛል። ካልሆነ ግን የማራዘም መብት የለዎትም። ሊራዘም ከማይችልባቸው ምክንያቶች ይህል፣ ለምሳሌ የወንጀል ቅጣት ወይም የሶሻል ድጋፍ ጥገኛ ከሆኑ ላይራዘም ይችላል። ያለማቋረጥ ከ6 ወር በላይ የውጭ አገር ቆይታ ካደረጉም ይህ የመቆያ ፈቃድ የአገልግሎት ግዜው ያበቃል። የስደተኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኙ ስደተኞችም ፈቃድ B ይሰጣቸዋል።
  • „የመኖሪያ ፈቃድ C“ (Niederlassungsbewilligung C): ይህ ፈቃድ የሚሰጠው ስዊዘርላንድ ውስጥ ከ5 ወይም 10 ዓመት በላይ ለቆዩ ነው። በተለይ ደግሞ ከEU/EFTA ሃገራት እንዲሁም ከሌሎች ሶስተኛ ሃገራት ለመጡ ነዋሪዎች የተለያዩ መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። ወደ ሌላ የውጭ አገር ቢሄዱ የተሰጠዎት የመኖሪያ ፈቃድ. እንደየሁኔታው ቢበዛ ለአራት ዓመት መቆየት ይችላል። ይህ እንዲሆን ግን በስደተኞች አስተዳደር ጽ/ቤት Migrationsamt ማመልከት ያስፈልጋል።
  • „ጊዝያዊ መቀበያ ፍቃድ F“ (Vorläufige Aufnahme F): ይህ ፈቃድ የሚሰጣቸው የስደተኝነት ጥያቄ ላመለከቱ ስደተኞች ሲሆን፣ እንደ ስደተኝነት ተቀባይነት ላላገኙ ስደተኞች ነው፣ ሆኖም በግዚያዊነት ለተመዘገቡት የሚሰጥ ፈቃድ ነው። ይህም ፈቃድ በየዓመቱ መታደስ አለበት።

የውጪ አገር ዜጋ መታወቂያ

በስዊዘርላንድ የሚኖሩ የውጪ ዜጋዎች የውጪ አገር ዜጋ (Ausländerausweis) መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መታወቂያ ይሰጣቸዋል። የሚሰጠው የመታወቂያው ዓይነት በተለያዩ መስፈርቶች ይወሰናል። ከውጭ አገር ወደ ጀርመን የሚመጡ ሰዎች የክሬዲት ካርድ ዓይነት ቅርጽ ያለው የባዮሜትሪክ መታወቂያ ካርድ ይሰጣቸዋል። በምዝገባው ግዜ የጣት አሻራቸው እንዲሁም የፎቶ ምስላቸው ይወሰዳል። መታወቂያቸው ቢሰረቅ ወይም ቢጠፋ ወድያውኑ በቅጽበት የግድ ለፖሊስ ማመልከት ያስፈልጋል። የጠፋብዎት መሆኑን ፖሊስ ያመለከቱበትን የምዝገባ ፎርም ማረጋገጫ እንዲሁም የአገርዎን የፓስፖርት ቅጂ ወይም (የEU/EFTA) ዜጋ ከሆኑ የመታወቂያ ወረቀትዎን በመያዝ አዲስ የመታወቂያ ወረቀት በስደተኞች አስተዳደር ጽ/ቤት (Migrationsamt) ማመልከትና ማዘዝ ይችላሉ።

ማራዘም

እንደ የመቆያ/የመኖሪያ/ ፈቃዱ ዓይነት እና እንዲሁም እንደ ዜግነትዎ ዓይነት እንደየሁኔታው በተለያየ ጊዜ የመቆያው /የመኖሪያው/ ፈቃዱ መራዘም አለበት። መራዘም ካለበት የማራዘሚያ ቅጽ /የማለቂያ ጊዜ ማሳሰቢያ/ (Verfallsanzeige) ይደርስዎታል። በዚህ በተላከሎት ቅጽ ላይ የስራ ቀጣሪዎ ማረጋገጥና መሙላት አለበት፣ በመጨረሻም የአገርዎ የጉዞ ፓስፖርት ቅጂ ወይም (የEU/EFTA) ዜጋ ከሆኑ የመታወቂያ ወረቀትዎን ከቅጹ ጋር በማያያዝ ለስደተኞች አስተዳደር ጽ/ቤት (Migrationsamt) መላክ አለብዎት።

በደንቡ መሰረት ዜግነት መቀየር

በስዊዘርላንድ ውስጥ ለአሥር ዓመታት የኖረ ማንኛውም ሰው ለፌዴራል የዜግነት ፈቃድ ዜግነት እንዲሰጠው ማመልከት ይችላል። ከ8 ዓመት ዕድሜው እስከ 18 ዓመት ዕድሜው ድረስ ስዊዘርላንድ ውስጥ የኖረ ማንኛውም ሰው የኖረበት ግዜ እጥፍ ሆኖ ይቆጠርለታል። ዜግነት ለማግኘት ተጨማሪ አስፈላጊ የሆኑ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች፣ የመኖሪያ ቦታ ገደብን ማሟላት፣ የጀርመንኛ ቋንቋ በቂ ችሎታ መኖር፣ ከማህበረሰቡ ጋር በጥሩ ሁኔታ መወሃሃድ እና ከዕዳ ነጻ መሆን ወይም ከወንጀል መዝገብ ነጻ መሆን ይጠበቅብዎታል።

በቀለለ መንገድ ዜግነትን መቀየር

በቀለለ መንገድ ዜግነትን ለመቀየር የተወሰኑ የህግ መስፈርቶች መሟላት አለባቸው፣ ከስዊዘርላንድ ዜጋ ጋር ጋብቻ የፈጸመ የውጭ ዜጋ እንዲሁም ከወላጆቹ አንዱ የስዊዘርላንድ ዜጋ ከሆነ ሰው የተወለደ ልጅ በቀላሉ ዜግነትን መቀየር ይችላል። በቀለለ መንገድ ዜግነትን ለመቀየር መወሰን የሚችለው የፌደራል መንግስቱ ብቻ ነው።