የግል የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ

ማንኛውም ዓዋቂ ሰው የግል የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ቢኖረው መልካም ነው። ይህንን ኢንሹራንስ የገባው ሰው፣ ሆነ ብሎ ሳይሆን በአጋጣሚ ጉዳት ቢያደርስ፣ ኢንሹራንሱ ወጪውን ይሸፍናል።

የግል ተጠያቂነት

አንድ ሰው በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢያደርስ ወይም የሌላ ሰው የሆነ ንብረት ቢያበላሽ፣ ይህ ሰው በግሉ በገንዘብ ተጠያቂ ይሆናል። የደረሰውን ጉዳት ሆነ ብሎ እንኳን ባይፈጸም፣ ይህ ሰው ተጠያቂ ይሆናል። ክፍያው በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በበረዶ ላይ መንሸራተት ስፖርት የሆነ ሰው ላይ ጉዳት ቢደርስበት፣ ጉዳቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ፍራንክ ሊደርስ ይችላል።

የግል የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ

አደጋ በሚደርስበት ግዜ የገንዘብ ችግር/ዕዳ/ ውስጥ ላለመግባት፣ የግል የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ (Privathaftpflichtversicherung)መግባት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ አብዛኞቹ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህንን አገልግሎት እንደሚሰጡ ያሳውቃሉ። አብዛኛውን ግዜ በአንድ ቤት ውስጥ በህብረት የሚኖሩ ሰዎች በአንድ ላይ የጋራ የግል የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ውል መፈጸም ይችላሉ። ይህንን ኢንሹራንስ መግባት ግን ግዴታ አይደለም፣ ይሁን እንጂ አጥብቆ ይመከራል።

ኢንሹራንሱ ምን ይሸፍናል

ኢንሹራንስ የገባው ሰው በሌላ ሰው ንብረት ላይ እና በሰው ላይ አደጋ ቢያደርስ፣ የግል የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንሱ ወጪውን ይሸፍናል። የሚሸፈነው ወጪ የጥገና ወጪዎችን፣ የህክምና ወጪዎችን፣ ለደሞዝ ኪሳራ ማካካሻ ወይም የአካል ጉዳት ካሳዎችን ያካትታል። የግል የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንሱ የተወሰኑ የቤት እንስሳዎች የሚያደርሱት ጉዳቶችን ኪሳራም ወጪ ይሸፍናል። አንድ ቤት ውስጥ በጋራ አንድ ላይ ከሚኖሩት ሰው ላይ ጉዳት ቢደርስ ኢንሹራንሱ የጉዳቱንና የኪሳራውን ወጪ አይሸፍንም። ኢንሹራንሱ ከማይሸፈኑናቸው ጉዳቶች መካከል፣ ጉዳቱ ሆነ ተብሎ ከተፈጸመ ወይም በግድየለሽነት አደጋው የደረሰ እንደሆነ ነው።