ባቡር፣ አውቶቡስ እና ትራም

በስዊዘርላንድ ውስጥ የህዝብ ትራንስፖርት በጣም የዳበረ ነው። እያንዳንዱ ትንሽ ከተማ በባቡር፣ በአውቶቡስ ወይም በትራም ተደራሽ ነው። የትራንስፖርት መጓጓዣዎቹ ሰዓታቸውን ጠብቀው በተወሰነ የጊዜ ልዩነት አገልግሎት ይሰጣሉ።

የሕዝብ ማመላለሺያ ትራንስፖርት

የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት (ÖV) በስዊዘርላንድ ውስጥ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል። አብዛኛውን ጊዜ በየሰዓቱ መድረስ ስለሚችሉ፣ በሁሉም ከተማ ያሉ ተጓዦች በባቡር፣ በአውቶቡስ ወይም በትራም ይጠቀማሉ፡፡ ጉዞዎቹ በአንጻራዊ ሁኔታ ውድ ቢሆኑም ገንዘብን ለመቆጠብ ብዙ አማራጮች አሉ። ስለዚህ የደንበኝነት ትኬት ወይም የቅናሽ ካርድ መግዛት ያዋጣል። በአንፃራዊነት ርካሽ በሆነው የግማሽ ታሪፍ ደንበኝነት ምዝገባ ካርድ (Halbtaxabonnement) ለምሳሌ በስዊዘርላንድ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ግማሹን ይከፍላሉ ።

ቲኬቶች እና የደምበኛ የውል ቲኬቶች

ባቡር ለመጠቀም የሚፈልግ፤ ከመጓዙ በፊት የመሳፈሪያ ትኬት (Billett) መግዛት አለበት። ቲኬቶች በባቡር ላይ መግዛት አይቻልም። ይህ በአውቶቡሶች እና በትራም ውስጥ በተለየ መንገድ ነው የሚተገበረው። በእያንዳንዱ የSBB ጣቢያ እና በአብዛኛዎቹ የአውቶቡስ ማቆሚያዎች የቲኬት ማሽኖች አሉ፣ እና በትላልቅ የባቡር ጣቢያዎችም ትኬት መሸጫ መስኮቶች አሉ። ቲኬቶችንም በመስመር ኦን ላይን ወይም በተንቀሳቃሽ ስልክ ሊገዙ ይችላሉ።
ብዙ ለሚጓዙ ሰዎች የተለያዩ የደምበኛ የኮንትራት ካርዶች አሉ። እነዚህ ለአንድ ጉዞ ብቻ፣ ለተወሰኑ መንገዶች፣ ወይም ለመላው የስዊስ ትራንስፖርት አውታር አጠቃላይ የኮንትራት ካርድ (Generalabonnement) አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። እስከ 6 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች በነጻ ይጓዛሉ። ዕድሜያቸው እስከ 16 ዓመት ድረስ የታዳጊ ወጣቶች ወይም የልጆች የጋራ የጉዞ ካርድ ካላቸው፣ ከወላጆቻቸው ወይም ከአያቶቻቸው ጋር በነፃ ይጓዛሉ። የቲኬቶች እና የደንበኝነት ምዝገባ ካርድ መረጃ ከስዊዘርላንድ ፌዴራል የባቡር ኩባንያ (SBB) ወይም ከትራንስፖርት ኩባንያዎች ማግኘት ይቻላል፡፡

የሰሜን ምዕራብ ስዊዘርላንድ የታሪፍ ማህበር TNW

የሰሜን ምዕራብ ስዊዘርላንድ የታሪፍ ማህበር በባዝል እና አካባቢው ለትኬቶች ልዩ ታሪፍ፣ የደንበኝነት ምዝገባዎች እና ዕለታዊ ትኬቶች ልዩ ዋጋ ይሰጣል። የTNW የመረብ አውታረ የሚገኙ አካባቢዎች በበርካታ ዞኖች የተከፈለ ነው። በሰሜናዊ ምዕራብ ስዊዘርላንድ ክልል በትራም፣ በአውቶቡስ እና በባቡር በተደጋጋሚ የሚጓዙ U-Abo ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። እና በድንበር አቅራቢያ ባሉ የውጭ ሀገራት ለሚጓዝ ሰው የተለየ ቲኬት ያስፈልገዋል።

የኮምዩኑ ዕለታዊ ትኬቶች

በስዊዘርላንድ ውስጥ ረዘም ያለ ጉዞ ለማድረግ ካቀዱ፣ በብዙ ኮምዩኖች ዕለታዊ ቲኬት (Gemeindetageskarte) በቅናሽ ዋጋ ማግኘት ይችላሉ። ነገር ግን ቅናሹ የተገደበ ነው፣ ቲኬቱን አስቀድመው ሪዘርቭ ማድረግ አለብዎት። በዚህ ላይ መረጃ ከነዋሪዎች ምዝገባ ጽ/ቤት ወይም ከኮምዩኑ አስተዳደር ጽ/ቤት ሊገኝ ይችላል፡፡

የሌሊት መስመሮች

ቅዳሜና እሁድ (ሌሊት ከአርብ እስከ ቅዳሜ ባሉት ምሽቶች እና ከቅዳሜ እስከ እሁድ ሌሊት) ትራሞች፣ አውቶቡሶች እና ባቡሮች በሌሊት በባዝል-ከተማ እና አካባቢው ይሰራሉ። ለTNW የሌሊት መስመሮች ተጠቃሚዎች ምንም ዓይነት ተጨማሪ ክፍያ አያስከፍልም።